በአዲስ ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ
ቀን 11/04/2015 ዓ.ም
በ2015 ዓ.ም የት/ት ዘመን የመጨረሻ ዓመት ላይ ሊተገበር በመንግስት እቅድ ተይዞ እየተሰራበት ባለው የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ፡፡
አዲስ ኮሌጅ ከትምህርት ሚኒስቴር ከመጡ የዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና ባለሞያዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ መድረክ የኮሌጁ አመራር አካዳሚክ ዲኖች የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተው ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ በትምህርት ሚኒስቴር የግል ከፍተኛ ት/ት ተቋማት ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር እዮብ አየነው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና የሚዳስስ እና ያለውን ልምድ ተግዳሮች እና ዕድልን (Assessing Higher Education Exit-Exam in Ethiopia Practices, Challenges and prospects) የተመለከተ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡ ሲሆን እንዲሁም በመስሪያ ቤቱ የጥራትና ብቃት ማረጋገጥ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰይድ መሐመድ የመውጫ ፈተና አስተዳደር እና ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ስርዓት አንፃር ያለውን መደላድል Exit-Exam (Administration and its premises in Ethiopian Higher Education System) የሚመለከት ገለፃ ቀርቧል፡፡
በዕለቱ ከቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፎች በተጨማሪ የከፍተኛ ት/ት የመውጫ ፈተና አፈጻጸም መመሪያ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመጡ ባለሙያ አቶ ፋሲል ፀጋዬ ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም በቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፎች እና ገለፃዎች ላይ የአዲስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኃላፊዎች መምህራን እና ተማሪዎች ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው ከመድረክ መልስ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዕለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ስለሺ መድረኩ ላይ ለመካፈል ለመጡት የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው ለወደፊትም ኮሌጁ የዚህ ዓይነቱን መድረክ በሚያዘጋጅበት ወቅት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ከባለሞያዎቹ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደማይለያቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡